አዲስ አበባ፣ ጥር 27 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢ.ፌ.ፖ.ሚ)፡-የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የፖሊስ ተሽከርካሪ የሰሌዳ ለውጥን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል::
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሎጂስቲስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ክቡር ረዳት ኮሚሽነር እሸቱ ፊጣ መግለጫውን በሰጡበት ወቅት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እያከናወነ ያለውን ሁሉ አቀፍ የሪፎርም ሥራ ተቋሙን ይበልጥ ለማዘመን ተሽከርካሪዎቹ ወጥ የሆነና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የሰሌዳ ሥርዓት እንዲኖራቸው ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል ።
አያይዘውም ከዚህ በፊት የነበረውን የተዘበራረቀና ወጥነት የሌለው የሰሌዳ አጠቃቀም ሥርዓት ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር በመሆኑ ይህንን አዲስ የሰሌዳ ስርዓት ታሪካዊ ያደርገዋል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ለህዝቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ፈጣን፣ ዘመናዊና ግልፅ በማድረግ ተጠያቂነትን የተላበሰ አሰራርን በማስፈን በፖሊስ ተሽከርካሪዎች አማካኝነት ምንም ዓይነት የዲሲፕሊን ጥሰት እንዳይፈፀም በተሟላ መልኩ ለመቆጣጠር የሚያስችል የሰሌዳ ስርዓት መሆኑንም ተናግረዋል ።
አዲሱ ሰሌዳ ዝም ብሎ ቀለምና ቁጥር ብቻ የተቀየረ ሳይሆን ከዘመናዊ የዲጂታል የመረጃ ቋት (Database) ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ለአሠራርና ለቁጥጥር ቀላል ያደርገዋል ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር ሰሌዳዎቹ በህገወጥ መንገድ የማይባዙ ከፍተኛ ሰኩሪቲ ያላቸው እና የደኅንነት መጠበቂያ ምስጢራዊ መለያዎች ያሏቸው መሆኑ ለየትኛውም የማጭበርበር ስራ ተጋላጭ እንዳልሆኑ ተናግረዋል ።
ይህ አዲስ የሰሌዳ ስርዓት ተቋሙን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቱን ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም ባሻገር የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ በቴክኖሎጂ ለመከታተልና ለሥራ አመራር ምቹ በማድረግ የወንጀል መከላከል ኦፕሬሽናል ስራዎችን በተፋጠነ፣ ፖሊሳዊ ስነምግባርን በተከተለ መንገድ መካሄዱን ለመከታተልና ለመቆጣጠር ብሎም አስፈላጊ ድጋፎችን ለማድረግ በከፍተኛ ደረጃ ይረዳል ብለዋል ።



